Joshua 23

ኢያሱ ለመሪዎች የተናገረው የመሰናበቻ ቃል

1 እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው እነሆ፣ ብዙ ዘመን ዐለፈ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በጣም አርጅቶ፣ ዕድሜውም ገፍቶ ነበር። 2ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ አለቆቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ፈራጆቻቸውንና ሹማምታቸውን በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቷል። 3አምላካችሁ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ሲል በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረገውን ማናቸውንም ነገር እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋላችሁ ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው። 4ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር
የሚድትራንያን ባሕር ነው።
ድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ።
5ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።

6“በርቱ፤ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ። 7በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር አትተባበሩ፤ የአማልክታቸውን ስም አትጥሩ፤ አትማሉባቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ 8ነገር ግን እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አጥብቃችሁ ያዙ።

9እግዚአብሔር ታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቷቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። 10አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት የሚዋጋላችሁ ስለሆነ፣ ከእናንተ አንዱ ሰው ሺውን ያሳድዳል። 11ስለዚህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለመውደድ ተጠንቀቁ።

12“ነገር ግን ከእርሱ ተመልሳችሁ ተርፈው በመካከላችሁ ከሚገኙት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ብትተባበሩ፣ በጋብቻም ብትተሳሰሩና ብትቀላቀሉ፣ 13አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ከፊታችሁ እንደማያወጣቸው ይህን ልታውቁ ይገባል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስም ወጥመድና አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ፣ ለዐይኖቻችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል።

14“እነሆ፤ አሁን የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሟል። 15ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁ መልካሙ ተስፋ በሙሉ እንደ ተፈጸመ ሁሉ፣ እንደዚሁም አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉውን ነገር ያመጣባችኋል። 16አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ኪዳን ብታፈርሱ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብትሰግዱላቸው የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ይነድዳል፤ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”

Copyright information for AmhNASV